You are here ታሪክና ስልጣኔ ኢስላማዊው ዓለም የረጀብ ወር ታላላቅ ክስተቶች

የረጀብ ወር ታላላቅ ክስተቶች

alt

የያዝነው ወር እንደ ሂጅራ አቆጣጠር ረጀብ ወር 1436 ነው። የረጀብ ወር አላህ ቁርአን ውስጥ ካከበራቸው አራት ታላላቅ ወራት መሀል አንዱ ነው። ረጀብ የሚለው ቃል ተከበረ፣ ተላቀ… የሚሉትን ትርጓሜዎች ይይዛል። ወሩ በዚህ ስያሜ የተጠቀሰው በጃሂሊያ ጊዜ ሰዎች ያከብሩትና ያልቁት ስለነበር ነው። ለርሱ ክብርም ጦርነት ይቆማል፤ ፍልሚያ አይፈቀድም። (አስ-ሲሓሕ ፊ አል-ሉጋ)

በዚህ ወር ውስጥ የተከሰቱ ታላላቅ የታሪክ አጋጣሚዎች አሉ። እነሱን በከፊሉ እነሆ፡-

 1. ኢስራና ሚዕራጅ፡- በዚህ ወር ሀያ ሰባተኛው ቀን ላይ የአላህ መልእክተኛ (ሰ.ዐ.ወ) ከመካ ከአጎታቸው ልጅ ቤት ወደ በይቱል መቅዲስ ፍልስጤም በለሊት ተጉዘዋል ወደ ሰማይም አርገው ተመልሰዋል። ጉዞው ተአምራዊ ጉዞ ነበር። እዚያም ያለፉት ነብያት ሁሉ ተሰብስበውላቸው ኢማም ሆነው አሰግደዋቸዋል። የርሳቸው የበላይነትና ክብርም ለፍጥረት ሁሉ ይፋ ሆነ።
 2. የተቡክ ዘመቻ፡- ዘጠነኛው አመት እንደ ሂጅራ በረጀብ አስረኛው ቀን የተከሰተ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ታላቅ ዘመቻ ነው።
 3. ነጃሺ (የሀበሻው ሙስሊም ንጉስ) ያረፉበት፡- ነጃሺ እስልምናውን እንደጠበቀ እንደ ሂጅራ ዘጠነኛው አመት በረጀብ ወር ውስጥ ሞተ። ነጃሺ (ረ.ዐ) በጣም መልካም ሠው ነበር። ታላቅ የአላህ ወዳጅም ነበር። በጃዕፈር ኢብኑ አቢጧሊብ (ረ.ዐ) መሪነት የመጀመሪያዎቹ የረሱል (ሰ.ዐ.ወ) ባልደረቦች ወደርሱ ተሰደዋል። ወደ እስልምናም ጠርተውት ከምርጥ ሙስሊሞች ሆኗል። የህልፈቱ ቀንም መልእክተኛው (ሰ.ዐ.ወ) የጋኢብ (የሩቅ የጀናዛ) ሶላት ሰግደውበታል።
 4. የየርሙክ ጦርነት፡- ይህ ጦርነት በሙስሊሞችና በሮማውያን መሀል የተካሄደው ረጀብ 5 ከሂጅራ በኋላ 15ኛው አመት ነበር። ይህም እ.አ.አ. ኦገስት 12፣ 636ን ይገጥማል። የየርሙክ ጦርነት ትልቅና ታሪካዊ ጦርነት ነበር። የጦርነቱ አሸናፊዎችም ሙስሊሞች ነበሩ። የጦርነቱ ውጤትም የሶሪያን ምድር ከማቅናት ጋሬጣ የነበረው የሮማውያን ክንድ መቆረጥ እና የሙስሊሞች ሀገርን የማቅናት ዘመቻ መጧጧፍ ነበር።
 5. ዐባስ ኢብኑ ዐብዱል ሙጠሊብ ያረፉበት፡- እንደ ሂጅራ ረጀብ 12፣ 32ኛው አመት ወይም እንደ ፈረንጆቹ ፌብሩዋሪ 16፣ 652 ላይ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አጎት ዓባስ ኢብኑ ዐብዱል ሙጦሊብ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ዓባስ የዳገቷ ስምምነት (በይዐቱል ዐቀባህ) ላይ ከነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ጎን የቆመ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) አጎት ነበር። መካ ከመከፈቷ በፊት ወደ መዲና መጥቷል። ነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ያከብሩት ነበር። ከአምስት ምእተ አመታት በላይ የሙስሊሙን አለም የገዛው የዐባሲያ ስርወ-መንግስት በዘር ሀረግ ወደርሳቸው ይጠጋል። የታላቁ ሶሀባና የቁርአን ተርጓሚ ዓብዱላህ ኢብኑ ዓባስ (ረ.ዐ) አባትም ናቸው።
 6. ታላቁ ኸሊፋ ዑመር ኢብኑ ዓብዱልዐዚዝ ያረፉበት፡- ዑመር ኢብኑ ዐብዱል ዐዚዝ በዚህ በያዝነው ወር ውስጥ 24ኛው ቀን ላይ እንደ ሂጅራ 101 አመት በሠላሳ ዘጠኝ አመታቸው አርፈዋል። ይህ አመት እ.አ.አ. ፌብሩዋሪ 6፣ 720 መሆኑ ነው። እኚህ ታላቅ ኸሊፋ በዕውቀታቸው፣ በተቅዋቸው፣ ከዱንያ ደንታ ቢስ (ዛሂድ) በመሆናቸውና በወልይነታቸው ይታወቃሉ።
 7. ኢማም አሽ-ሻፊዒይ ያረፉበት፡- ኢማም አሽ-ሻፊዒይ በሀምሳ አራት አመታቸው እንደ ሂጅራ ሁለት መቶ አራት ላይ በዚሁ ወር ውስጥ ሞተው ግብፅ ውስጥ ተቀበሩ። ይህ ቀን እ.አ.አ. ጃንዋሪ 20፣ 820 ነው። እኚህ ኢማም በሀገራችን በስፋት የሚገኘው የሻፊዒያ መዝሀብ መስራች መሆናቸው ይታወቃል። “የቁረይሽ ዓሊም ምድርን በሙሉ በዒልም የሚሞላት አለ።” የሚለው የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሀዲስ (ቲርሚዚ ውስጥ የተዘገበው) እርሳቸውን ለማለት እንደሆነ ብዙዎች ይስማማሉ። ፍልስጤም (ጋዛ) ውስጥ ተወልደዋል። ከዚያም ዒራቅ፣ መካ፣ መዲና እና ግብፅ ውስጥ ኖረዋል። ግብፅ ውስጥም ተቀብረዋል።
 8. አስ-ሲዩጢይ ውልደት፡- ረጀብ 1 እንደ ሂጅራ 849 አመት ላይ ታላቁ ዐሊም ጀላሉዲን ዐብዱራህማን ቢን አቢበክር (ጀላሉዲን አስ-ሲዩጢይ) ተወለዱ። እኚህ ዐሊም ታላቅ የፊቅህ፣ የሐዲስ፣ የቋንቋ፣ የተፍሲር፣ የታሪክ እና ዐቂዳ (እምነት) ምሁር ናቸው። “ጀምዑል ጀዋሚዕ”፣ “ሑስኑል ሙሐደራ”፣ “አድዱሩል መንሱር”፣ “አል-አሽባህ ወንነዟኢር”… እና ሌሎችም ታላላቅ ድርሰቶች አሏቸው።
 9. ኢብኑል ቀዪም ያረፉበት፡- ታላቁ ዓሊም ዐብዱላህ ሙሐመድ ኢብኑ ቀዪም አልጀውዚያ ረጀብ 23፣ 751 እንደ ሂጅራ ወይም እ.አ.አ. ሴፕቴምበር 26፣ 1350 ላይ አርፈዋል። እኚህ ታላቅ ዓሊም ከስምንተኛው ምዕተ አመት (ሂጅራ) እንደ ዓይኖች የሚቆጠሩ ነበሩ። ሐዲስ፣ ፊቅሂ፣ ታሪክ እና ተሰዉፍ ላይ በፃፏቸው መፅሀፍት ይታወቃሉ።
 10. ሶላሑዲን አል-አዩቢይ ቁድስን ያስመለሰበት፡- ረጀብ 27 ከሂጅራ በኋላ 583 ላይ (እ.አ.አ. ኦክቶበር 2፣ 1187) ሙስሊሞች በሰላሑዲን አልአዩቢይ መሪነት ወደ ተነጠቀችው የተከበረችው የቁድስ ከተማ ተመለሱ። ቁድስ ከዚህ በፊት ለሰማንያ ስምንት አመታት ድረስ በመስቀለኞች በወረራ ተይዛ ነበር። ሶላሑዲን ቁድስን የተቆጣጠሩት ሂጢን የተባለችው ሥፍራ ላይ ታላቅ ድል ከነሳ በኋላ ነው። ድል አድራጊው መሪ ወደ ቁድስ ሲገባ የመስቀል ጦረኞች በሙስሊሞች ላይ የፈፀሙትን እስካሁን አለምን የሚያሳዝን ፍፁም አሰቃቂ ደም የማፍሰስ ድርጊት እነርሱ ላይ አልፈፀመም። እንደውም ይቅር አላቸው። በነፃነት እንዲኖሩም አደረገ።
 11. የቱርክ መንግስት በአታቱርክ መሪነት፡- ኣያ በተባለው ጥንታዊ መስጊድ ውስጥ ሶላት እንዳይሰገድ እና ውስጡ ያሉት መስገጃዎች፣ በዓረብኛ የተፃፉ ጥንታዊ የሎህ ፅሁፎችና ሚንበሩ ወጥቶ ለሶፊያ መዘክር እንዲሰጡ እና መስጊዱ ለቱሪስት መስህብነት እንዲውል አረመኔያዊ ውሳኔ አስተላልፏል። ይህም የሆነው ረጀብ 16፣ 1353 እንደ ሂጅራ ወይም ፌብሩዋሪ 21፣ 1925 ነበር።
 12. የመጨረሻው ኢስላማዊ የኸሊፋ ስርአት ተጣለ፡- ይህ ክስተት ረጀብ 27፣ 1342 እንደ ሂጅራ ወይም ማርች 1924 እ.አ.አ. ነበር። ስርአቱ የኦቶማን የኸሊፋ ስርአት ነበር። የወደቀውም በሙስጦፋ አታቱርክ እጅ ነበር። ከዚያም አታቱርክ እራሱን የቱርክ ፕሬዝዳንት አድርጎ ሾመ። የዑስማኒያን (ኦቶማን) ኸሊፋና ቤተሰቡን ከሀገር አባረረ። ሙስሊሞቹ በኸሊፋው መመራት ቢሹም አታቱርክ መብታቸውን ነፈገ። በዚህም ምክንያት አኮብኩበው የነበሩት የቅኝ ግዛት አውሮፓዊያን በሙስሊሞች መሀል የነበረውን የመንፈስ ትስስር መበታተን ቻሉ። ለአመታት ያለሙት ህልምም ከብዙ ልፋት በኋላ ተሳካላቸው።
 13. የቱርክ መንግስት (በአታቱርክ መሪነት) ቁርአን በዓረብኛ ቋንቋ ሳይሆን በቱርክ ቋንቋ እንዲነበብ አዘዘ፡- ይህ ግፍ የሆነው ረጀብ 28፣ 1344 ወይም እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ፌብራሪ 21፣ 1925 ነበር።
 14. አቡል አዕላ አልመውዱዲይ ውልደት፡- የፓኪስታኑ ጀመዓህ ኢስላሚያ መስራች አቡል አዕላ አልመውዱዲ ረጀብ 3፣ 1321 ወይም እ.አ.አ. ሴፕቴምበር 25 1903 ተወለዱ። ሰውየው ከዚህ ምእተ አመት (እንደ ሂጅራ) ታላላቅ የዳዕዋ ሰዎች መሀል የሚጠቀሱ ናቸው። ቁርአንን ለመገንዘብ፣ የነብዩ (ሰ.ዐ.ወ) ሲራ (የህይወት ታሪክ)፣ “ተፍሂመል ቁርዐን”- ተፍሲር እና ሌሎች ጠቃሚ ድርሰቶች አሏቸው።
 15. አሕመድ ዲዳት ያረፉበት፡- ታላቁ የዘመናችን የዳዕዋ ሰው በሰማንያ ሰባት አመታቸው በዚህ ወር፣ ደቡብ አፍሪካ በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ነበር የሞቱት። ቀኑም እንደሂጅራ ረጀብ 3፣ 1426 ሲሆን እ.አ.አ. ኦገስት 8፣ 2005 ነበር። ዲዳት የተወለዱት ረመዳን 22፣ 1336 እንደ ሂጅራ ወይም ጁላይ 1፣ 1918 እ.አ.አ. ህንድ ውስጥ ነበር። ከዚያም ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተዋል። ብዙዎችን ወደ እስልምና የመለሱባቸው የኃይማኖት ውይይቶችና ክርክሮች ዲዳትን ያስታውሱናል። ዲዳት በእስልምናና ክርስትና መሀል ምርጫ፣ እውን መፅሀፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ነው? እና መሰል መፅሐፍትን ለኃይማኖቶች ውይይት አለም አበርክተዋል።

Share this post

ተያያዥ ርዕሶች

Comments  

 
-1 #6 Abduselam 2014-05-10 19:23
JezakAllah!!
Quote
 
 
0 #5 Abdu Rehman 2014-05-02 21:18
H
Quote
 
 
+3 #4 Bilal H 2013-05-17 21:32
Jezakellah!!, may allah help u to do more, inshallah, keep it !!!
Quote
 
 
+2 #3 miftah 2013-05-14 19:49
bettam teqamy yehonu merejawoch nachew

jezakumullah

yih website eskahun kayehuacew bestu new

jezakumullah
( yezewetr teketatayachu)
Quote
 
 
+3 #2 abdulaziz ibrahim 2012-06-03 05:32
Allahuakeber
Quote
 
 
+3 #1 abdulaziz ibrahim 2012-06-03 05:29
Allahuakeber!!! !
Quote
 

Add comment


Security code
Refresh